የኢሚግሬሽን መብቶች እና የመረጃ ግብዓቶች ማዕከል

ለመጨረሻ ጊዜ የተሻሻለው፡- እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 22 ቀን 2025

ማሳሰቢያ:- ይህ ሰነድ ለትምህርት፣ ለሲቪክ እና ለመብት ሙግት ዓላማዎች እንዲያገለግል ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በዚህ ድረ ገፅ ላይ የሚገኝ ማንኛውም ነገር እንደ የሕግ ምክር ሊታሰብ ወይም ሊወሰድ አይገባም፡፡ ምንም እንኳን የሕግ ምክር መስሎ ቢታይም፣ እያንዳንዱ ሁኔታ የተለያየ ስለሆነ፣ እርስዎ ላሉበት የተለየ ሁኔታ እንዲያገለግል ታስቦ የተሰጠ የሕግ ምክር አይደለም። እርስዎ ላሉበት ልዩ የኢሚግሬሽን ሁኔታ የሚጠቀም የሕግ ምክር ከፈለጉ፣ እባክዎን ለዚህ ስራ ብቁ የሆነ ጠበቃ ያማክሩ።

ሁለተኛው የትራምፕ አስተዳደር በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የጅምላ እስር እና ከአገር የማባረር መርሃ ግብርን ጨምሮ ሰፊ የኢሚግሬሽን ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። እነዚህ ፖሊሲዎች የስደተኛ ቤተሰቦችን እና ማህበረሰቦችን ዒላማ ያደርጋሉ፣ የሕግ ማስከበር እርምጃዎችን ይበልጥ ያጠናክራሉ፣ እንዲሁም ዜጋ ላልሆኑ ሰዎች የሚሰጥ ከለላን ያዳክማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ስደተኞች ከዚህ ቀጥሎ እንደተዘረዘሩት ያሉ ከባድ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ መዘጋጀት አለባቸው፦

  • ከአገር እንዲወጡ የመጨረሻ ትዕዛዝ የወጣባቸው ወይም የወንጀል ሪከርድ ያለባቸው ግለሰቦችን ዒላማ ያደረገ ጠንካራ ከአገር የማባረር እርምጃ።
  • የስደተኞች ከለላ ይደረግልኝ ጥያቄን ተቀብሎ ለማስተናገድ ይበልጥ አስቸጋሪ የሆኑ ጥብቅ የጥገኝነት ጥያቄ ማስተናገጃ ፖሊሲዎች።
  • አስፈሪ በሆነ የኢሚግሬሽን ሕግ ማስከበር ስራ አማካኝነት ስደተኞች በማህበረሰቡ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲገታ ማድረግ።

የኢሚግሬሽን ሁኔታዎ ምንም ይሁን ምን፣ በዩኤስ ሕገ መንግስት ዋስትና የተሰጣቸው መብቶች አሉዎት። መብቶችዎን ማወቅ እና ሊከሰቱ ለሚችሉ ለውጦች መዘጋጀት እራስዎንና ማህበረሰብዎን ለመጠበቅ ወሳኝ እርምጃዎች ናቸው። መብቶችዎም ከሕገ ወጥ ፍተሻዎች እና በቁጥጥር ስር ከማዋል ከለላ ማግኘትን፣ ዝም የማለት መብትን፣ ጠበቃ ለማነጋገር ጥያቄ የማቅረብ መብትን እና በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ወይም ከአገር ሊባረሩ ከተቃረቡ በሕጉ መሠረት ፍትሃዊ አያያዝን የሚያረጋግጡ የተወሰኑ ሕጋዊ ዋስትናዎችን የማግኘት መብቶችን ያካትታሉ። በቤትዎም ይሁን በሥራ ቦታዎ ወይም በአደባባይ፣ እነዚህን መብቶች መገንዘብ እና እንዴት ማስጠበቅ እንደሚችሉ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው።

ከትራምፕ አስተዳደር ምን ይጠበቃል

በሁለተኛው የትራምፕ አስተዳደር ወቅት በኢሚግሬሽን ፖሊሲ ላይ ጉልህ ለውጦች ይጠበቃሉ። እነዚህ ለውጦችም ቀደም ሲል በመጀመሪያው የትራምፕ አስተዳደር ስር የተዘረዘሩ እንደ ኢራን፣ ናይጄሪያ እና የመን ያሉ ሀገራትን ያነጣጠረ የጉዞ እገዳ ወደነበረበት መመለስን ሊያካትቱ ይችላሉ። በተጨማሪም የጉዞ እገዳዎቹ እንደ ቻይና እና ህንድ ያሉ ሌሎች አገሮችን በማካተት ሰፋ ተደርገውም ሊተገበሩ ይችላሉ። ለጥገኝነት ጠያቂዎች በሚሰጡ ከለላዎች ላይ ተጨማሪ ጥብቅ ገደቦች ሊጣሉ እንደሚችሉ እና እንደ ወደ ሀገር ውስጥ ለገቡ ሰነድ አልባ ልጆች ይሰጥ የነበረው የህግ ከለላ (DACA) እና ጊዜያዊ ከለላ የሚያሰጥ የኢሚግሬሽን ሁኔታ (TPS) ያሉ ፕሮግራሞች ሊወገዱ ይችላሉ። በጅምላ ከአገር የማባረር እርምጃዎች፣ ምንም እንኳን ሕግ ነክ ውጣ ውረዶች እነዚህን እርምጃዎች ሊያዘገዩ የሚችሉ ቢሆንም ከአገር እንዲባረሩ የመጨረሻ ትዕዛዝ የወጣባቸው ወይም የወንጀል ሪከርድ ያለባቸውን ግለሰቦች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ያለ ወላጅ ወይም ህጋዊ አሳዳጊ ብቻቸውን ወደ አገር ውስጥ በገቡ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ሕፃናት እና ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ሕፃናት ይዘው ወደ አገር ውስጥ ለገቡ ቤተሰቦች ይሰጡ የነበሩ ከለላዎች ሊዳከሙ ይችላሉ፣ ይህም የቤተሰብ ደኅንነትን ለማስጠበቅ አስቀድሞ ማቀድን እና ግለሰቦች ስለሚይዙት ሰነድ በጥንቃቄ ማሰብ አስፈላጊ መሆኑ ላይ አጽንዖት ይሰጣል። ዓለም አቀፍ ተማሪዎች እና ሠራተኞች ለተጨማሪ የቪዛ ጥያቄ ምላሽ መዘግየት እና የማንነት ማጣሪያ ፍተሻዎች መዘጋጀት አለባቸው፣ እናም ተፅዕኖው ይጎላባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ክልሎች የሚጓዙ ግለሰቦች ሴሚስተሩ ከመጀመሩ በፊት ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ ይመከራል። በተጨማሪም፣ ከእነዚህ ፖሊሲዎች በስተጀርባ ያሉ ጠንካራ የህዝብ ፖሊሲ አመክንዮዎች ቢኖሩም፣ ህጋዊ ከለላ በሚደረግላቸው ቦታዎች እና/ወይም ህጋዊ ከለላ ይደረግላቸው በነበሩ ተግባራት ላይ በሚወሰዱ አንዳንድ የህግ ማስከበር እርምጃዎች ወቅት ቀደም ሲል ገደብ ይጥሉ የነበሩ ፖሊሲዎች ሊሻሩ ይችላሉ። እነዚህም በልጆች ላይ የሚደርሰውን እንግልት መቀነስ፣ የጤና አገልግሎት ማግኘትን እና የአምልኮት ተግባራትን የመፈፀም መብት ማክበርን ያካትታሉ።

የቀጣይ ጎዳና፡- ቅድመ ዝግጀት እና የማህበረሰብ ጉልበት/ኃይል

እነዚህ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ ቅድመዝግጀት ማድረግ ተስፋን የሚያለመልም ሲሆን ጉልበትም/ኃይልም አለው። የሕግ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች፣ የጋራ መረዳጃ ቡድኖች፣ እና የመብት ተሟጋች ኔትወርኮች በእነዚህ ፈታኝ ጊዜያት ስደተኞችን ለመርዳት የሚያስችሉ ግብዓቶችን በማቅረብ ረገድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በንቃት ይሰራሉ። የቤተሰብ አስቸኳይ ጊዜ እቅድ ማዘጋጀት፣ ከፈጣን ምላሽ ሰጪ ኔትወርኮች ጋር መገናኘት እንዲሁም ስለ ሕጋዊ ጉዳዮች መረጃን በንቃት መከታተል ቁልፍ ስልቶች ናቸው። ኤጀንሲዎች እና መስሪያ ቤቶች፣ እንዲሁ፣ ሠራተኞችን በማሰልጠን፣ የድርጊት መርሃግብሮችን በማዘጋጀት፣ እና ለሰራተኞች እና ለአገልግሎት ተቀባዮች ፖሊሲዎችን እና ሂደቶችን በማብራራት፣ የቅደመ ዝግጅት ስራዎችን መደገፍ ይችላሉ። እያንዣበበ ያለው የሥጋት ዳመና እውነት ነው፣ ነገር ግን የእኛ ጉልበት እና አይበገሬነትም እንዲሁ ነው። የቤተሰብ መለያየት ፖሊሲን በመቀልበስ ረገድ፣ ህዝባዊ እምቢተኝነት እና አደረጃጀት ጎጂ ፖሊሲዎችን ለመቃወም ከዚህ ቀደም ውጤታማ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በጋራ ይህን ጊዜ መጋፈጥ እንችላለን። እሴቶቻችንን መከላከል እንችላለን። ኃይላችንን ማሳየት እንችላለን። ማህበረሰባችንን መጠበቅ እንችላለን።

የመፃኢ ጊዜ ምልከታ፡- ሁለተኛው የትራምፕ አስተዳደር

የሕግ እና የሎጂስቲክስ ውጣ ውረዶች ቢኖሩም የመጀመሪያው የትራምፕ አስተዳደር የኢሚግሬሽን ሕግ ማስከበር ስራን በማጠናከር ይታወቅ ነበር። ከዚህ በፊት እንዳየነው ግልጽና ወጥ የሆነ" መብትህን እወቅ" ስልጠና እና ጠንካራ የማህበረሰብ ጥምረት ስደተኞችን ትርጕም ባለው መንገድ ሊከላከሉ ይችላሉ።

አሁን ምን ማድረግ ይችላሉ?

  1. በንቃት መረጃዎችን ይከታተሉ፡- ህጎች እና ፖሊሲዎች በፍጥነት ሊለዋወጡ ይችላሉ። እንደ ACLU National Immigration Law Center (NILC), Catholic Legal Immigration Network, Inc. (CLINIC), ወይም አካባቢዎ እንደ ሚገኝ የድጋፍ ሰጪ ቡድን ያሉ ታማኝ ድርጅቶችን ይከታተሉ።
  2. እቅድ ያዘጋጁ፡- የህግ ማስከበር እርምጃዎች መወሰድ ከጀመሩ የአስቸኳይ ጊዜ እውቂያ ዝርዝር፣ ሕጋዊ ሰነዶች፣ እና የቤተሰብ እንክብካቤ እቅድ ዝግጁ ያድርጉ።
    1. ሰነዶችን አስተማማኝ በሆነ ቦታ ያስቀምጡ፡-
      1. ማንነትዎን የሚገልፁ እና የፋይናንስ መረጃዎችዎን ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ያስቀምጡ።
      2. በዩናይትድ ስቴትስ የቆዩበትን የጊዜ ርዝመት የሚጠቁሙ ሰነዶችን ይሰብስቡ፤ የመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት በጣም አስፈላጊ ናቸው። ይህም የዩኤስ የገቢ ግብር ተመላሾችን፣ የፍጆታ ሂሳቦችን፣ ኪራይ፣ የትምህርት ቤት መዝገቦችን፣ የህክምና መዝገቦችን፣ የባንክ መዝገቦችን ወይም ሌሎች ሰነዶችን ሊያካትት ይችላል።
      3. የአደጋ ጊዜ ተጠሪዎ እነዚህን ሁሉ ሰነዶች ማግኘት መቻሉን ያረጋግጡ።
  3. ከመሰል አጋሮች ጋር ይገናኙ፡- በአካባቢዎ የሚገኙ የመብት ተሟጋች ኔትወርኮችን፣ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድኖችን ወይም መርጃዎችን እንዲሁም ድጋፍ የሚሰጡ የበጎ ፈቃድ ቡድኖችን ይቀላቀሉ